ይቅር አለማለት: ክፍል 1

በሰዎች ተጎድተን ያዘንንበት ወቅት ሊኖር ይችላል። በደረሰብን በደል ምክኒያት አዝነናል፣ ልባችን ተሰብሯል ፥ ተጨንቀናል ፥ ስሜታችን ተጎድቶ በሃዘንና በንዴት ፥ ምናልባትም በምሬት ተሞልተናል። የበደሉ ጥልቀት ፥ “በደሉን´´ ከምንላቸው ሰዎች ጋር የነበረን ቅርበትና ከእነርሱ የነበረን ጥባቆት ከፍ ያለ ከሆነ መጎዳታችንን የከፋ ያደርገዋል። በተለይ ደግሞ ያሳዘኑን ሰዎች የቅርብ ሲሆኑ ፤ የታመኑ ፥ ዘመድ ወዳጅ ፥ የቅርብ ጓደኛ ፥ “እነርሱን ለመርዳት ዋጋ ከፍለንባቸዋል´´ ብለን ስናስብ ወይም ብዙ የምንጠብቅባቸው ሲሆኑ ጉዳቱን ጥልቅ ያደርገዋል። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ሲበድሉን ይቅር ልንላቸውም የማንፈልግበት ደረጃ የምንደርስበት ጊዜያት ጥቂት አይሆኑም።

ከደረሰብን በደል በተጨማሪ ይቅር አለማለታችን ደግሞ ውስጣችንን እየቦረቦረ ፣ የተበደልን ሆነን ሳለን ከፍ ወዳለ መጎዳት ውስጥ ይጥለናል። ማቴዎስ ወንጌል 18:-21-35 ተበድለን ይቅር ስላለማለት የሚያስተምረን አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ በመሆኑ እንመልከተው።

ይህ ክፍል መበዳደልን አስመልክቶ በአማኞች መካከል ሊከሰት የሚችለውን ይቅር አለማለትንና ጠንቁን ያስረዳል። የቃሉን ፍሰትና ቀደም ያሉትን ቁጥሮች ጨምረን ስንመለከት ፤ በአማኞች መካከል ያለ ጉዳይ መሆኑን የሚያመላክቱ በርካታ ሃሳቦችን እናገኛለን። ጌታ ኢየሱስ “ወንድምህም ቢበድልህ´´ እያለ መናገሩ፤  “ሌሎች ርምጃዎችን ወስደህ ባይሰማ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት´´ ማለቱ ይህንን ያረጋግጣል። ከጴጥሮስ ጥያቄ ስንነሳ ደግሞ  “ጌታ ሆይ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜን?´´ ማለቱ ፤ የጌታ ኢየሱስም ምላሽ የሚናገረው ስለመንግስቱ ባህሪያት መሆኑና የአማኞችን  የማሰርና የመፍታት ስልጣን ጭምር የሚገልጽ በሆኑ በአማኞች መካከል ሊከሰት የሚችል እኛንም የሚመለከት ሆኖ ይገኛል ።  

ወደ አንዳንድ የንግድ መስሪያ ቤቶች ተቆጣጣሪዎች ባልታሰበና ባልተገመተ ወቅት ድንገት ይመጡና መጋዘኑን አሽገው ፥ የስራውንም ቦታ ዘግተው ቁጥጥር ይጀምራሉ። ስራው በትክክል መሰራቱን ፣ የሒሳብ ስራው ትክክለኛ መሆኑንና ማንኛውም ንብረት ያለመጉደሉን ያመሳክራሉ። ያ ሳይሆን ሲቀር ግን የሚመለከተውን ሰው እስከ እስር ቤት በመላክ ማጣራታቸውን ይቀጥላሉ። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሰውዬ በፍርድ ቤት ውሳኔ ከቅጣት ጋር ዕዳውን እንዲከፍል ይደረጋል። ይህም ቅጣት እስርን ሊያካትት ይችላል።

በማቴዎስ ወንጌል 18:-21-35 የሂሳብ መዝገቡን ለማዘጋት ንጉሱ ሲቆጣጠር እልፍ መክሊት ዕዳ ያለበት ሰው ፊቱ ይቀርብለታል። ይህ ዕዳ እጅግ ከፍተኛና ተከፍሎ የማያልቅ ገንዘብ ቢሆንም ሰውዬው ራሱ ፥ ሚስቱና ልጆቹ እንዲሁም ያለው ሁሉ እንዲሸጥና ጥቂትም ቢሆን ከዕዳው እንዲከፍል ንጉሱ አዘዘ። ሰውዬው ግን እግሩ ስር ወድቆ “ንጉስ ሆይ ያለብኝን ዕዳ ሁሉ እከፍላለሁ፣ ብቻ ጊዜ ስጠኝ´´ ሲል ለመነው። ንጉሱም ርህሩህ ነበርና አዝኖ በነጻ ለቀቀው። ዕዳውን በጭራሽ መክፈል እንደማይችል ስለሚያወቅ ሙሉ በሙሉ ተወለት ፥ ምህረትም አደረገለት።

ዕዳው የተተወለት ይህ ባሪያ ከንጉሱ ተሰናብቶ ከወጣ በኋላ ፤ የሱ ትንሽ ዕዳ ያለበትን ሌላ ባሪያ አገኘ። ሄዶም “ዕዳህን ክፈለኝ´´ ብሎ ያዘና አነቀው። ባልንጀራውም “ሁሉን እከፍልሃለሁ ብቻ ጊዜ ስጠኝ´´ ብሎ እርሱ ንጉሱን እንደለመነ ለመነው። ሆኖም ግን ሰውዬው አልወደደም። ገንዘቡ ጥቂትና የሚከፈል ቢሆንም እዳውን እስኪከፍል ድረስ ወስዶ በወህኒ አኖረው።

እያንዳንዳችን ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ፤ በበደላችንና በሐጢያታችን ምክኒያት ሞት ያውም የዘላለም ሞት የሚገባን ነበርን። ነገር ግን እግዚአብሔር ለምህረቱና ለፍቅሩ ወሰን የሌለው አምላክ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ይቅር አለን ፥ የሚቃወመንን የዕዳ ጽሕፈት ደምስሶ ከመንገድ አስወገደው። እንዲሁ በጸጋው አዳነን። ታዲያ ወሰን የለሽ ይቅርታ ተደርጎልን ፥ የማይገባንን ምህረት ተቀብለን ሳለ ምነው ጥቂት የበደሉንን ይቅር ማለት አልፈለግን?

ሰውዬው የማይከፈል ዕዳውን ይቅር በመባሉና ምሕረት በማግኘቱ ሐሴት እያደረገ በምስጋና ሊኖር ሲገባው ፤ የእርሱ ሊከፈል የሚችል ጥቂት ዕዳ ያለበትን ሰው ማነቁ ምን ይባላል? በርግጥ ተበድሎ ሊሆን ይችላል። ሕጉም ሊፈቅድለት ይችል ይሆናል። ግን ካገኘው ምህረት አንጻር ሲታይ ይህ እንደ ምንም የሚቆጠር ነበር። ይባሱንም እስኪከፍለው ድረስ ወስዶ በወህኒ ቆለፈበት። እስር ቤትስ መገረፍ ይኖር ይሆን? ምን ዓይነት ክፉ ሰው ነው ብለን ከመፍረዳችን በፊት ግን እጅግ ብዙ ይቅር የተባልነው እኛ ስለበደሉን ሰዎች ምን ያህል ተናግረናል? በምላሳችን አለንጋችንስ አልገረፍናቸውም? በስንቶቹ ላይስ ልባችንን ቆልፈንባቸዋል?  

በብዙ ወንጀል የተለያዩ እስር ቤቶች ታስሮ የነበር ፤ ኋላ ግን በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ የዳነ አንድ ወንድም “በዓይነትም በጥራትም የተለያዩ ብዙ እስር ቤቶችን አይቻለሁ ፤ ከሁሉም ግን እጅግ የከፋው ይቅር የማይል ልብ ነው።´´ ብሏል። አዎን ይቅር አለማለት ሰውን በእስር ቤት ቆልፎ ማስቀመጥ ነው። ነገር ግን የምናስረው ሌሎችን ሳይሆን ራሳችንን ነው። ይቅር አለማለት አዕምሮአችንን ይይዛል ፥ ደስታችንን ይነጥቃል ፥ ሰላማችንን ይገፋል ፥ እንቅልፋችንን ይነሳናል ፥ በአጠቃላይ ጤናችንን ይጎዳል።

በተጨማሪም ይቅር አለማለት በሁለት ግለሰቦች መካከል ብቻ የሚያበቃ ጉዳይ አይደለም። በተለይ ጊዜው እየገፋ በሄደ ቁጥር አካባቢ ላይም ተጽዕኖ ይፈጥራል።   አካባቢን የሚያምስ ፥ ሌሎችንም የሚነካ፥ ለሐሜትና ለአሉባልታም ጭምር በር ከፋች ይሆናል። አዎን ይቅር አለማለት ዙሪያን ይበክላል ፥ ይነካል ፥ ይጎዳል ፥ ያሳዝንማል። አልፎ ተርፎ ሲብስ በወንድማማች ፥ በወዳጆች ፥ በዘመድ፥ በቤተሰብ፥ በቅዱሳን መካከል እስከ ቤተክርስቲያን ድረስ መከፋፈልን የሚያስከትል ይሆናል። ይቅር አለማለት ከእግዚአብሔርም ከሰዎችም ጋር ያለንን ሕብረት ያበላሻልና።

የሰውዬው ድርጊት ሌሎች ባልንጀሮቹን እጅግ አሳዘናቸውና መጥተውም ነገሩን ለጌታቸው ገለጡ። ጌታውም ተቈጣ ፤ ሰውየውንም አስጠርቶ “ያንን ሁሉ ስፍር ቁጥር የሌለውን ምሕረት አግኝተህ አንተስ ባልንጀራህን ለምን አልማርከውም?´´ ብሎ ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍለው ድረስ ለሚሣቅዩት አሳልፎ ሰጠው። ፈጽሞ ሊከፈል የማይቻል ዕዳ! እኛስ የተቀበልነውን ፍቅር ፥ ያገኘነውን ምሕረት ፥ የተዋጀንበትን የኢየሱስ ደም የሚመጥን ምን ክፍያ ይኖረናል? ስለምንስ ጌታ ያዝንብናል? በራሳችን ላይስ ስለምን ቁጣውን እናነሳሳለን?

ይቅር አለማለት እግዚአብሔር የሰጠንን ትዕዛዝ መቃወምም ነው። በቆላስይስ ሰዎች 3፥13 “እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤´´ ይላል። “እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ´´ (ኤፌሶን 4፥32) ::በዚህ ባነበብነው ክፍል መጨረሻ ላይ ጌታ ኢየሱስ “ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፥ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል።´´ አለን። ደረሰብን ከምንለው በደል ይልቅ ፤ በሕይወታችን የተገለጸውን የእግዚአብሔር ፍቅርና ምሕረቱን እናሰላስል። ለራሳችን ብለን ለበደሉን ሰዎች ይቅርታ እናድርግ። አለበለዚያ ግን ይቅርታን አናገኝምና። ስንጸልይ “እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን´´ አይደል የምንለው? በድለውህን ይቅር ያላልካቸው ሰዎች ይኖሩ ይሆን? ታዲያ ምን ልታደርግ አስብህ?

አዎን ይቅር አለማለት ይቅርታ እንዳናገኝ ያደርገናልና በይቅርታ እንመላለስ።

  • ጥያቄ 1.  ይቅርታን ማድረግ የችሎታ ጉዳይ ነው ወይስ የፈቃድ?
  • ጥያቄ 2. ደጋግመው እየበደሉን ይቅርታ ስለሚጠይቁን ሰዎችንስ ምን እናድርግ?
Tesfaye Mekonen
Tesfaye Mekonen
Facebook
Twitter