astronomy
TESFAYE MEKONEN

TESFAYE MEKONEN

CREATION

የአጽናፈ ዓለም አመጣጥ

አካባቢያችንን ስንመለከት የተለያዩ ግዑዛንና የሚንቀሳቀሱም ሆነ የማይንቀሳቃሱ ሕይወት ባላቸው ተሞልቶ እናገኛለን። ሰማያትን ስናስብ ደግሞ አዕምሯችንን በበለጠ መደነቅ ይሞላል። እነኚህ ሁሉ ከየትና እንዴት እንደመጡ ለማወቅ በየዘመኑ የነበሩ ሰዎች የተለያዩ ሃሳቦች ሰንዝረዋል። በአጠቃላይ ስለ አጽናፈ ዓለም አመጣጥ ሰዎች “ደረስንበት´´ ብለው ከሚሰጡት መደምደሚያዎች ውስጥ ከተለያዩ ቀላል ተረት-ተረቶች ጀምሮ ብዙ አፈታሪኮችም ይገኙበታል። በርካታ ሃይማኖቶችና ፍልስፍናዎችም የተለያዩ አስተሳሰቦችንና እምነቶችን ይዘውልን ይቀርባሉ።
ሆኖም ግን ከእነኚህ ፍልስፍናዎች፥ አስተሳሰቦችና እምነቶች ውስጥ ሥር ሰደውና ብዙ ተቀባይነት ካላቸው ውስጥ ሁለቱ ዋነኛ የሆኑት የአዝጋሚ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ Theory of Evolution ና የሰነ ፍጥረት አስተምህሮ- The Doctrine of Creation ናቸው።

  1. የአዝጋሚ ለውጥ ጽንሰ ሃሳብThe Theory of Evolution

እንደ አጠቃላይ የአዝጋሚ ለውጥ ጽንሰ ሃሳብ (Theory of Evolution) አመለካከት ሕይወት ከሌላቸው ነገሮች በአጋጣሚ ቀላል ሕይወት ያለው የመጀመሪያው ህዋስ በድንገት ከአንድ ሂደት የተነሳ እንዳስገኘና ያ ህዋስ ራሱን እያባዛ እንደሄደ፥ እነኚህም ህዋሳት ደግሞ በሚሊዮን ዓመታት ውስጥ በተለያዩ ምክኒያቶች በየግዜው በሚመጡ ትንንሽ ለውጦች ክምችት ቀስ በቀስ ያደጉ ፍጥረታትን እንዳስከተሉ ይናገራሉ። እንደነሱ አባባል ሰውንም ጨምሮ ፍጡር ሁሉ የተገኘው ከቀላል ወደ ውስብስብነት በሚጓዝ አዝጋሚ ለውጥ ሂደት ነው።

የአዝጋሚ ለውጥ ጽንሰ ሃሳብ Theory of Evolution በዚህ ዘመን በጣም ትኩረት የተሰጠውና አደገኛ የሆነ ፍልስፍና ሲሆን ብዙ የተለያዩ አመለካከቶች ያካተተ ነው። ሆኖም ግን ሁሉም የጋራ አስተምህሮና ዓላማ አላቸው።

ዋናውም የወል ትምህርታቸው የሁሉ ፈጣሪ የሆነውን የእግዚአብሔርን ህልውና መካድ ነው። ዋና ዓላማቸው መጽሐፍ ቅዱስን መቃወም፥ ፈጣሪ የለም ማለት ሲሆን ያ ደግሞ ሃላፊነትና ተጠያቂነት የለምና መልካም መስሎ የታየህን አድርግ ሲሉ ለሞራልና ለእውነት ምንም ስፍራ የላቸውም።
ይህንንም ብዙ ማስረጃዎች ናቸው የሚሏቸውን ነገሮች በመደርደር ለማሳመን ይጥራሉ አንድ ሰው“ውሽትን በብዙ ዓይነት መንገድ፥ ካለመታከት ለረጂም ግዜያትና በብዙ ስፍራዎች ከተናገርህ ሰዎች እውነት ነው ብለው ይቀበሉሃል።´´1 ብሎ እንደተናገረ ይነገራል።
ለዚህም መሳካት መንግስታትና የተለያዩ ድርጅቶች ከፍተኛ በጀት መድበዋል። ሐሰተኛ የሐሰት አባት2 ማን መሆኑን መጽሀፍ ቅዱስ በግልጽ አስቀምጦልናል።

እንደ አጠቃላይ ኢቮሉሽን ተከታዮች አጽናፈ ዓለም የፍንዳታና የአዝጋሚ ለውጥ ሂደት ዕድገት ነች።
ሁለት ነገሮች ድንገት፥ በአጋጣሚና በዕድል ተጋጩና ዓለማት ተፈጠሩ። ከዛም የዛሬ 4.5 ቢሊዮን ዓመታት መሬት ተገኘች። ከ3 ቢሊዮን ዓመታት በፊት በአጋጣሚ፥ በድንገትና በዕድል ህይወት ከሌለው ነገር አንድ ህዋስ (ሴል) ያለው ህያው ነገር በምድር ላይ መጣ።
ያም በሚሊዮን ዓመታት ቀስ በቀስ ራሱን እያባዛ ሄዶ የጀርባ አጥንት የሌላቸው እንሰሳትን አስገኘ። ከዛም ከብዙ ሚሊዮን ዓመታት በኋላ ከእነኚህ የጀርባ አጥንት የሌላቸው እንሰሳት አዝጋሚ ለውጥና የተፈጥሮ ምርጫ >>> ዓሶች ተገኙ። ከሌላ ብዙ ሚሊዮን ዓመታት በኋላ ደግሞ እነኝህ ዓሶች >>> በውሃና በምድር መኖር የሚችሉትን እንሰሳት (Amphibians) አስገኙ በዛው መንገድ >>> በደረታቸው የሚሳቡት (Reptiles) >>> ቀስ በቀስ ከብዙ ሚሊዮን ዓመታት በኋላ አጥቢዎችን (Mammals) ያም ቀሰ በቀስ እየተለወጠ >>> ሰው መጣ ይላሉ። እንደነርሱ አባባል የሰው ልጅም በእግዚአብሔር የተፈጠረ ሳይሆን የዛሬ 3.5 ሚሊዮን ዓመታት በፊት በአዝጋሚ ለውጥ የተገኘ ነው።
ስለዚህ ሰው ያለ ዕቅድ መጣ፥ ያለ ዓላማ አለ ፥ ያለ ግብ ይኖራል ፥ መድረሻ  የለውም ማለት ነው።

ይህ የዝግመተ- ለውጥ ፍልስፍና ሃሳብ ቀደም ብሎ የነበረ ቢሆንም ገኖ የወጣውና የተንሰራፋው ግን ከ1850 ዓም በኋላ ነው። ለዚህም ትልቅ ተጽዕኖ ያደረገው ቻርለስ ዳርዊን Charles Darwin ነው። ዳርዊን The Theory of Evolution by means of natural Selectionን አስመልክቶ በ1859 ዓም “The Origin Of Species“ የሚል መጽሐፉን ጻፈ። እንደ ዳርዊን “The survival of the fittest by means of natural selection´´ ወይም “የተፈጥሮ መረጣ´´ አባባል ፤ በዚህ አዝጋሚ ለውጥ ሂደት ምርጦቹና የተሻሉት በሕይወት ሲኖሩ ሌሎቹ ደግሞ እየጠፉ ሄደዋል። በዚህም መሰረት ከተሻለ ዘር ተወልዶ የተሻለ ሆኖ ፥ በልጦ መገኘት ለህልውና ወሳኝ ነው።
የኢየሱስ ትምህርት ትህትና ፥ ራስን ዝቅ ማድረግ ፥ የዋህነት ፥ ደግነትና አገልጋይ መሆን ወዘተ ሰውን ደካማ የሚያደርግ፥ የማያሳድግ ፥ ኋላ የሚያስቀርና የሚያስጠቃ ነው። ደካማውን ከማገዝ ይልቅ እንዲጠፋ ማድረግ ፤ አዲስ የተሽለ ዘር እንዲመጣ ተፈጥሮአዊ ክንዋኔንና አዝጋሚ ለውጥን ማፋጠን ሊሆን ነዋ! ይህም መረጣ በቀለም፥ በጎሳና በዘር ማጥፋት ዘመቻዎች ላይ ያደረገው አስተዋጽዖ ቀላል አይደለም።

እንዳውም Ernest Haickel ና መሰሎቹ “ የአፍሪካውያን ኢቮሉሽን ገና ኋላ ቀር በመሆኑ አዕምሮቸው እድገቱን አልጨረሰም´´ ይሉናል። Wayne Grudem በመጽሐፋቸው3  የዝግመተ-ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ እንደሚለው ሰው ያለፈጣሪ የመጣ፥ ያለ ዓላማና እቅድ በእድልና በአጋጣሚ ከተገኘ ፤ እንዲሁም ያለ ግብ የሚኖር ከሆነ፥ የሰው ሕይወት ምን ፋይዳ አለው? እርባና የሌለን ፍጡራን እንደሆንን ማሰቡ ራስን ወደ ተስፋቢስነት የሚያመራ ትልቅ ስህተት ማዘጋጀት መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ የአዝጋሚ ለውጥ ፍልስፍና ከመዋዕለ ህጻናት ጀምሮ በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞች ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ በከፍተኛ ጥረት እንዲካተት ተደርጓል። Adolf Hitlerም “የስርዓተ ትምህርት መጽሃፍትን ከተቆጣጠርኩ፥ አገርን መቆጣጠር ቀላል ይሆንልኛል።´´ ብሏል።
ያንንም ለማከናወን ከፍተኛ በጀት የተመደበ ሲሆን ልጆቻችን በሄዱበት ቦታ ሁሉ ያለማቋረጥ የሚሰሙት ይህንኑ ነው። ይህ ሁሉ ያላሰለሰ ጥረት የሚደረግበት ምክኒያት ከልጆችና ከወጣቶች አእምሮ ፈሪሃ እግዚአብሔርን አስውጥቶ እግዚአብሔር የለም´´ በሚል ክህደት ለመተካት ነው። የዚህን ጥረት አዝማሚያ በራሱ ዘመን የተመለከተው ማርቲን ሉተር “የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ተገልጦ በወጣቶች ልብ ካልተቀረጸ በስተቀር የትምህርት ተቋሞች የሲዖል በር ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል ይኖራል ብዬ እፈራለሁ።“ ብሏል።
ይህም በልጆችና በወጣቶች ላይ ከፍተኛ አፍራሽ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ተጽዕኖ አሳድሯል፥ በማሳደርም ላይ ይገኛል። አሁንማ ከስርዓተ ትምህርቱ ጎን ለጎን በቲቪ፥ በተለያዩ ህብረተሰባዊ መገናኛዎች ወዘተ ያለማቋረጥ ይጠቀጥቋቸዋል። እያደር ይበልጥ እየከፋ እንጂ እየተሻለ እንደማይሄድ ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህ ፈጣሪ የለም የሚለው ፍልስፍናቸው ደግሞ ጠያቂ የለምና እንዳፈለጋችሁ ኑሩ፥ የፈለጋችሁን የማድረግ ነጻነት አላችሁ4 ወደሚለው ሞራልና ስነምግባር የጎደለው ሕይወት ያመራል።

Evolution አደገኛና ጸረ-እግዚአብሔር የሆነ ፍልስፍና በመሆኑ፥ ዲሞክራሲና በመሳሰሉት ስም እግዚአብሔር የደነገጋቸውን መለኮታዊ ሥርዓቶችና መዋቅሮችን የማፈራረስ አጀንዳ አለው።
ይህንንም ድብቅ ተልዕኮአቸውን ለማሳካት ሲታገሉ ይገኛሉ። ከእነኚህም ውስጥ ጸረ ቤተሰብ በሆነው አቋማቸው ፥ ቤተሰብ ማዕከላዊ ዒላማ በመሆኑ ከፍተኛ ጥቃት እየደረሰበት ይገኛል።

                      **** ይቀጥላል****

1. Adolf Hitler 

2. የዮሐንስ ወንጌል 8፥44  

3.Systematic Theology. An Introduction to Biblical Doctrine

4. 2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2፥19   

ይህ ጽሁፍ በጉተንበርግ የኢትዮጲያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን የጸጋ ሥነ መለኮት ት/ቤት በ TH 102  ለመግቢያ ተጨማሪ ይሆን ዘንድ ከተጻፈው የተወሰደ ነው።

Share this post