Fruit of the Holy Spirit

በመንፈስ ፍሬ እንመላለስ ክፍል 1

በገላትያ መልእክት ምእራፍ 5 ላይ የሥጋ ሥራና የመንፈስ ፍሬ ምን እንደሆኑ በዝርዝር ተገልጾ እናገኛለን።
የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ መዳራት፥ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። (ገላ 5÷19-21)


የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው።” (ገላ 5÷22)

ከዚህ ከላይ የተዘረዘሩትን መንፈሳዊ ባሕሪያትን ፍሬዎች ብሎ ከመጥራት ይልቅ ”ፍሬ” በሚል ነጠላ ቃል ተገልጿዋል። በነጠላ ቃል የተጠቀሰበት ዋናው ምክንያት ዘጠኙም ባሕሪያት አንድነትና ስምምነት ያላቸው እንደሆነ ከማሳየቱም በላይ ሁሉም በአንድ ፍሬ ውስጥ ተጠቃልለው ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያንጸባርቁ በመሆናቸው ነው።

የክርስቶስን ባሕሪ በውስጣችን የሚፈጥረው መንፈስ ቅዱስ ነው። የእውነተኛ ክርስቲያን ባሕሪ መገለጫ የሆነውን የመንፈስ ፍሬ በአማኞች ሕይወት ውስጥ እንዲገለጥ የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ ነው። ማንም ሰው ባለው በሰብአዊ ማንነቱ የተነሳ የመንፈስን ፍሬ ማፍራት አይችልም። ይህ እንዲሆን ግን አንድ ሰው ሕይወቱን መንፈስ ቅዱስ እንዲቆጣጠረው ሊፈቅድ ይገባል። መንፈስ ቅዱስ እንዲቆጣጠረን ፈቀደኛ ስንሆንና ለእርሱ በተሰጠን ቁጥር በባሕሪያችንና በኑሮአችን ከቀድሞ ይልቅ ኢየሱስ ክርስቶስን እያንጸባረቅን እንሄዳለን። አንድ አማኝ ያለው መንፈሳዊ እድገትና ብስለቱ የሚለካው በሕይወቱ ውስጥ በሚታየው መንፈሳዊ ፍሬ ልክ ነው። ፍሬው በሕይወታችን እንዳደግንና እንደበሰልን የሚያሳይ ምልክት ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን እንደሞተና በአሸናፊነትም እንደተነሳ እኛም እንዲሁ  አሮጌው ማንነታችን ከእርሱ ጋር ተቀብሮ በትንሣኤው ሕያው ሆነናል። በክርስቶስ ዳግም ስንወለድ እርሱን የምንመስልበት ሰማያዊ ዘር ወይም መለኮታዊ ባሕሪ ተሰጥቶናል። በውስጣችን የተቀመጠው መለኮታዊ ባሕሪ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚያስችለንን ነገር ሁሉ አብሮ እንደሰጠን የእግዚአብሔር ቃል ያስረግጥልናል። 

2 ጴጥ 1፡3 ”በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን እርሱን በማወቅ ለሕይወትና ለእውነተኛ መንፈሳዊነት የሚያስፈልገንን ሁሉ የመለኮቱ ኃይል ሰጥቶናል።”
የተጠራነው ኢየሱስ ክርስቶስን እንድንመስል ነው። ክርስቶስን እንድንመስል ደግሞ መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ በብርቱ ይሰራል።

ሮሜ 8፡29 ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና”
ክርስቶስን ለመምሰል ምን ማድረግ አለብን? ብለን የጠየቅን እንደሆነ መልሱ ሁለንተናችንን መንፈስ ቅዱስ እንዲቆጣጠረው አሳልፈን እንስጥ የሚል ይሆናል። ይህም በጸሎት፣ ቃሉን በማጥናት፣ ከቅዱሳን ጋራ ኅብረት ማድረግ፣ ወዘተ በትጋት በማድረግ ነው።

በሁሉም አማኞች ላይ የመንፈስ ፍሬ እንዲታይ የእግዚአብሔር የሁልጊዜ ፍላጎትና ናፍቆት ነው። የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ በአማኞች ሕይወት ውስጥ እንዲገለጥ የእግዚአብሔር ፈቃድ ቢሆንም እንኳ ይህ ሊሆን ደግሞ የሚችለው አንድ አማኝ እንደሚመርጠው ምርጫ ነው። ለታላቅ ክብር እንደተጠራን ገብቶን ለዚያ እንደሚገባ እንድንኖርና እንድንመላለስ የጌታ ቃል በብርቱ ያስገነዝበናል።

ኤፌ 4፡1 …በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ•

አንድ አማኝ የእግዚአብሔርን ባሕሪ ለማንጸባረቅ ያለው ፈቃድና ድርሻ ከፍ ያለ እንደሆነ በበርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ የተጠቀሰ ቢሆንም እንኳ በኤፌሶን መጽሐፍ ላይ የተገለጹትን ሁለት ጥቅሶች ብቻ ወስዶ መመልከት በቂ ነው።

ኤፌ 4፡24 … እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።
ኤፌ 4፡24 …የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ።

የመንፈስ ቅዱስ ፍሬና የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች የተለያዩ ነገሮች ናቸው።

  • በሕይወታችን የመንፈስ ፍሬ ሲገለጥ የክርስቶስ ባሕሪ በሁሉ ዘንድ እንዲታይ እናደርጋለን። በተለይ ደግሞ ዓለም ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስን በቀላሉ የሚያዩት በሕይወታችን መንፈስ ፍሬ ሲኖር ነው። በዚህም ሁኔታ የጌታ እውነተኛና ብቁ ምስክሮች ሆነን እንቆጠራለን።
  • የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች የሚሰጡት ግን የክርስቶስ ቤተክርስቲያን በዚህ ምድር ላይ የምታበረክተውን መንፈሳዊ አገልግሎት በብቃት መፈጸም እንድትችል ነው።

የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ ከመንፈስ ፍሬ ውጪ ውጤታማ ሆኖ ሊታይ አይችልም። ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ምእራፍ 12 ላይ ስለ መንፈሳዊ ሥጦታዎች ከፍ ያለ ትንታኔ ከሰጠ በኋላ “ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ” በማለት በምእራፍ 13 ላይ የመንፈስ ፍሬ ስለሆነው ስለ ፍቅር ሰፊ ማብራሪያ ይሰጣል።

1 ቆሮ 13፡1-3, 8-10 “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም።” “ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል። ከእውቀት ከፍለን እናውቃለንና፥ ከትንቢትም ከፍለን እንናገራለንና፤ ፍጹም የሆነ ሲመጣ ግን ተከፍሎ የነበረው ይሻራል።”

የጸጋ ስጦታ ለእያንዳንዱ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስ እንደ ወደደ የሚሰጠው ስጦታ ሲሆን የመንፈስ ፍሬ ግን አንድ አማኝ በክርስቶስ ውስጥ ሲኖር ብቻ የሚያሳየው ሕይወት ነው።  የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እንዲኖረን እንደምንፈልግና እንደምንተጋ ሁሉ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ እንዲታይብን በብርቱ ልንሻ ይገባል።አንድ አማኝ የተሰጠው መንፈሳዊ ስጦታ በዘላቂነት ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያደርገው በሕይወቱ የሚታየው የመንፈስ ፍሬ ነው። የጸጋ ስጦታ ያለ መንፈሳዊ ፍሬ ውጤታማ አይደለም። ለምሳሌ፦ የቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በብርቱ ይሰራ ነበር። ሆኖም ግን በምእመናኑና በአገልጋዮቹ ላይ የመንፈስ ፍሬ ይታይ ስላልነበረ በርካታ ችግሮች ተከስተው ነበር።

የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ለቤተክርስቲያን ሲሰጡ መልካም ነው። በዚያው አንፃር ደግሞ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውበት በዓለም ሁሉ ላይ ጎልቶ እንዲታይ በአማኞች ሕይወት ውስጥ የመንፈስ ፍሬ ሊገኝ ይገባል። የመንፈስ ፍሬ ከጸጋ ስጦታዎች ጋር ተጣምሮ ሲሰራ ትልቅ ውጤት ያስገኛል። አለዚያ ግን ብዙ ሰዎች የእግዚአብሔር መንግሥት የሚስባቸውና የሚያጓጓቸው አይሆንም። የመንፈስ ፍሬ የምናፈራ ቢሆን ሌሎች ሰዎች በእኛ ውስጥ የልጁን (ክርስቶስን) መልክ በቀላሉ ማየት ይችላሉ። አንድ ሰው እድገትና ብስለት ሳይኖረው የጸጋ ስጦታዎች በአንድ ጊዜ ሊሰጡት ይችላሉ። የመንፈስ ፍሬ ግን ሥር የመስደድ፣ የማደግና የመብሰል ውጤት ነው።  

ወደ ላይ — ወደ እግዚአብሔር፣

ወደ ጎን — ወደ ቅዱሳን ሁሉ ጋር

ይቀጥላል …

Pastor Dawit
Pastor Dawit

Senior pastor for Ethiopian evangelical church in Gothenburg Sweden

Facebook
Twitter

This Post Has 3 Comments

  1. Reta Shiferaw

    Wow, great message “ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን እንደሞተና በአሸናፊነትም እንደተነሳ እኛም እንዲሁ አሮጌው ማንነታችን ከእርሱ ጋር ተቀብሮ በትንሣኤው ሕያው ሆነናል። በክርስቶስ ዳግም ስንወለድ እርሱን የምንመስልበት ሰማያዊ ዘር ወይም መለኮታዊ ባሕሪ ተሰጥቶናል። በውስጣችን የተቀመጠው መለኮታዊ ባሕሪ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚያስችለንን ነገር ሁሉ አብሮ እንደሰጠን የእግዚአብሔር ቃል ያስረግጥልናል። “

  2. Meron

    Such a great teaching Pastor!
    የመንፈስ ፍሬ ግን ሥር የመስደድ፣ የማደግና የመብሰል ውጤት ነው።  As Believers, we are called to become more Christ-like in our thoughts, hearts, minds, and actions. One great practical thing I took from this reading is that, I need to first identify and acknowledge the areas in which I am the weakest in order to deepen my relationship with Jesus and allow the holy spirt to shape me more after his own heart. The sanctifying power of Christ can cures any spiritual weakness that hinders fruits of the spirit in our life. So thank you for this message pastor, it’s very important topic and a wake up call!
    May God bless you more! I can’t wait to read more on this platform!!

    1. Reta

      Well said Meri!!
      “The sanctifying power of Christ can cures any spiritual weakness that hinders fruits of the spirit in our life. So thank you for this message pastor, it’s very important topic and a wake up call!”
      The only thing expected from us is to release ourselves to the Holy Spirit to work in us, we need to allow him to transform us into christ like

      Bless you more

Comments are closed.